Sost kilo

ባለኮኮቡ ፓስቲኒ !


Listen Later

የዛሬ ሃያ ዓመት ገደማ ፤ በሆነ በማይታወሰኝ ቀን ከእንቅልፌ ተነስቼ ስንገላጀጅ የግንፍል ሾርባ ሽታ አፍንጫዬን ሰርስሮ ገባ ። ቅንድቦቼን በፍትጊያ አላቅቄ አነፈነፍኩ ' የፈጣሪ ያለህ ፓስቲኒ ነው ። '
ከስጋ ቀጥሎ የምር የምጠላውና - የሚጠላኝ መብል ፓስቲኒ ነው ። የዶሮ መረቅ ቢገባበትማ ራሴን ሲጥ አርጌ የማጠፋ ይመስለኛል ። ሰባት ዓመቴን ልደፍን የቀሩኝ ቀናት ቢሆንም ዛሬም እናቴ ያለሱ ቁርስ ያለ አይመስላትም ። አሰራሩ ቀላል ሆኖ ይሁን ቶሎ ስለሚደርስ እንጃ የቤታችን የጠዋት ጠዋት ሜኑ ሁለት ነው ። የተሰራልህን ፓስቲኒ ወደህ ፤ ወይ ደሞ የተሰራልህን በግድህ ትበላለህ ።
ከአልጋዬ ወርጄ በባዶ እግሬ ወዳለችበት ስሄድ እናቴ ደመኛዬን ከመቀቀያው ወደ ሣህኑ ስትገለብጠው ደረስኩ ። የኪሮስን ' ሠላም ሠላም ሓዋ ' ከፍ አርጋ ከቴፑ እኩል ትዘፍናለች ። ወላ እስከጊታሩ . . . ድሪሪን ዲዲሪን ተቐልቀሊ . . . ዲሪሪ . . . ፈውሲ ክረኽብ . . . ድሪን ድሪን ።
ደቃቅ ካሮት እና ብትን አረንጓዴ ቅመም ቤዡ ሾርባ ላይ ፈጠው ይታያሉ ። " ዛሬም ፓስቲኒ ነው አደል ? እኔ አልበላልሽም ! ከማክሰኞ ጀምረሽ እያለቀስኩ አስጋትሺኝ ። ትንሽ እንኳ ግን አታስቢልኝም ? "
ብሶቴንን ባልሰማ ገፍታ ' ቦንጆርኖ ! ተነሳሽ ጌታው ? ' አለች ሆጵ አርጋ አንገቴን እየሳመች ። ' ማዐረይ እቺን ጭርስ አርገህ ብላ እንጂ የማረግልህን አታውቅም ? ' የዘወትር ማባበያዋን እንደ አዲስ አነበነበችልኝ ። እኔ ብትሰማኝና ብታደርግ ደስ የሚለኝ ይሄን ሾርባ በጭራሽ መስራት ብታቆም ነው ።
" ደሞ አዲስ የቬሮና ፓስቲና ነው ቀድጄ ያረኩልህ - መሀሉ ላይ ክብ ያለው ኮኮብ - የኮኮቦች ምግብ ነው - እንዴት እንደሚጥም አንተ ራስህ ነው ምትነግረኝ ። ሂድ ጫማህን አርገህ ና - ረፍዷልኮ ፤ ዳይ ! "
ከፓስቲኒው በላይ የሚረብሸኝ የእናቴ የጠዋት ጠዋት ፍጥነት ነው ። ገና በወጉ ሳልነቃ ቡናዋን እስከሶስት ትልስና ቁርሳችንን አብስላ ፤ ትቀሰቅሰኛለች ። በቅጡ ባልነቃ አይኔ አያታለሁ ፤ ቤቱ ውስጥ እንደተርብ ጥዝዝ'ዝ ትላለች ። እኔ ገና አንድ ነገር ሳልናገር ወለል ወልውላ ጥ...ዝ ፤ ሻይ ጥዳ ጥ...ዝ ፤ ሸሚዟን ተኩሳ ጥ...ዝ ፤ ቦርሳዋን ዘርግፋ መልሳ ትከታለች ። ጥዝታዋን ስትጨርስ እንደሮቦት እያሽከረከረቺኝ ዩኒፎርም ታስለብሰኛለች ። እጅህን ከፍ አርገው ፤ እስኪ ዙር ፤ እስኪ ደሞ እየኝ . . . ቤሎ - ቤሎ ! ልዕሎም ናተይ - በል ና እንሂድ ።
የኪራይ ቤታችን ውስጥ ያለነው እኔ ማማና ድመታችን 'ፍቅሪ' ብቻ ነን ። ፍቅሪ ፋንዲሻ እየበላች ፓስቲኒን ግን አሽታ ነው የምተወው - እንደኔው ። የቤታችን ብሶት ዋነኛ ምንጭ የማማ ሥራና ውሎ ከጣልያኖች ጋር መሆን ነው ። በፊት ምግባቸውን ስላንገፈገፈኝ እነርሱንም ( ፓስቲኒ በሊታዎቹን ) ጠልቼ ነበር ። ይሄ ጥላቻዬ በባለፈው ቅዳሜ ግሪጎሪ በላከልን የራሊ ግብዣ በአንድ ጀምበር ተነሳ ። የመኪና ራሊውን ካየሁ አንስቶ ወሬዬ ሁሉ ከኢምቤርቶና ከሮቤርቶ ባዛኒ ማን ይቀድማል ሆነ ። እናቴም አድቫንቴጁን ወስዳ ቅዳሜ አብዮት አደባባይ መሄድ ከፈለክ እሷን በልተህ ጨርስ እያለች ሳምንቱን ሙሉ አስወጠቀችኝ ።
ዛሬ ፓስቲኒውን በቀስም ብስበው ራሱ እሺ ብሎኝ የሚገባልኝ አልመሰለኝም ። ጠረጴዛው ላይ ነጭ ማንኪያና ጎድጓዳውን ባለአበባ ሣህን ስታኖር የዘቢት ፈገግታ ሰጠኋት ። " እንደነገርኩህ ነው የዛሬው ይለያል ፤ ቀልጢፍካ ብላዕ ሽኮር " ብላ የፀጉሯን ማስያዣ እየፈታች ወጣች ። ያለወትሮዋ ነው ። ሁሌም ቁርሴን ትቀርብና እስካጠናቅቅ ድረስ እያየች ቀይ ቀለም የተቀቡ ጥፍሮቿን ጠረጴዛው ላይ ታንቋቋቸዋለች ። ቋቋታው ከማንኪያው ላይ ስወስድ ካለው ስ...ፕታ ጋር ሲደመር የራሱ ዜማ አለው ። የሆነ ስቅጥጥ የሚል ፤ ዋጣት የሚል ፤ የሚያንገሸግሽ አይነት - ቋኴ♪ቋኴ ስ♫ፕ ቋኴ♪ቋኴ ስ♫ፕ ቋኴ♪ቋኴ ስ♫ፕ 🎶 ።
ማማ ረጅም ቀሚሷን እያንሿሿች ስትወጣ ከፓስቲኒው ጋር ለብቻችን ቀረን ፤ ተያየን ። አናቴ ጀርባ ካለች ኩርቢት የተንጠለጠለች ባጆዬን እያስፈተልኩ ብዙ አሰብኩ ። በዚህ ጭንቅ መሀል ሆኜ ወንበር ስር የተቀረቀረ ባለ ረጅም ሂል ቡትስ አይኔ ገባ ። አ. . . ሃ ጭንቅላቴን እያሰራሁት ነው ፤ ይሄን ጫማ ስለሚጠባት ይሁን ስለማትወደው ብዙውን ግዜ አታረገውም ። መፍትሄ ሊሆን ይችላል ፤ እንዴት ?
ፓስቲኒውን የአግድም ይዤ ጫማው ውስጥ አንቆረቆርኩት ። ስጨርስ የሣህኑን ጠርዝ ላስኩና አፌን ጠራረግኩ ። የቡትሱ ኣፍ ላይ የተንጠባጠበውንም ሾርባ በሹራቤ አፅድቼ ወደናቴ ሮጥኩ ።
' ማማ ትንሽ ጨምሪልኝ ' የከንፈር ሰም እየቀባችው የነበረውን ከንፈሯን ከፍታ አየችኝ ፤ ግማሹ እንደቀለመ ነው ። አስተያየቷ ሲረዝም . . . አውቃለሁ እናቴ ! ግርምትሽ ይገባኛል - ሰው እኮ ሁሌ እንደምታስቢው አይሆንም ። ይለወጣል ፤ ይሻሻላል ልላት ፈለኩ ።
አይኗን ሰበረችና ' አየህ ሁሌ እንዲህ ከበላህ ጠንካራ ትሆናለህ ። ' ከመዳፌ ወረድ ብላ እጄን በሁለት ጣቷ ከባ እያሳየች. . . ' ይሄን ትሞላዋለህ ። የክፍላቹን ትልቋ ልጅ ማናት ስሟ'ማ . . . አዎ : ሳሮን'ን ወላ ትበልጣታለህ ' አለች ። እናቴ በምግብ እንዲህ ትደሰታለች ብዬ አስቤ አላውቅም ። እንደሳሮን ግን መሆን አልፈልግም ። ሙሉ የአጋዚያን ተማሪ ፉስቶ ነው የሚላት ፤ ፉስቶ መባል ማን ይፈልጋል ።
ጨራርሰን - ቦርሳዬን አስነግታኝ ልክ ልንወጣ ስንል የት ነበር ያልተባለ ካፍያ በሰያፍ መጣል ጀመረ ። ማማ ' ቆይ - እንዳትወጣ ዣንጥላ ልያዝ ' ብላ ወደውስጥ ተመልሳ ገባች ።
በአለላ ቀለም ያሽቆጠቆጠ ዣንጥላዋን ከወሸቀችበት ስታወጣ ከቡትሷ ፊትለፊት ጋር ተያዩ ። አይኖቼ ሰፉ ፤ ጣቴ ቆልፌ ቦርሳዬን እንዳዘልኩ ራድኩ ። ቡኒ ቡትሷን አይታ ያደረገችውን ጥልፍልፍ ሰንደል ገርመም ስታረገው የስንብድ በጮክታ ተናገርኩ ' ኧረ ተይ ረፈደብን ' ።
' አየሩ ጥሩ አይደለም አንተም ኮፍያ ያለው ጃኬትህ አርግ ' ብላ ጫማዋን በቁሟ ፈታ የቀኝ እግሯን ቡትስ ለማጥለቅ ትታገል ጀመር ። ሰቀቀን ገላዬን አኮማተረው ። የቀኟን እግሯን በዚፗ ወደላይ ሾጥ አርጋ አጠበቀች ። ግራዋን እንደማንሳት ስትል ጀርባዬን ሳላዞር ወደበሩ አፈገፈግኹ ።
ጭምር ስታረገውና እግሯን ሲረጥባት አንድ ሆነ ። እንደመብረር ባለ አቋቋም ሆና አይኖቿ ፈጠጡ ። በሩ ከፍቼ እየሮጥኩ ወጣሁ ። ካፊያው እየወረደብኝ ቀጭን ጩኸትና ስድብ ሲከታተሉ ሰማሁ . . .
ዋ...... ይ ! ማማሚያ - ኼ ካቮሎ!
[ Leoulzewelde.wordpress.com ]
...more
View all episodesView all episodes
Download on the App Store

Sost kiloBy Leoul Zewelde

  • 4.8
  • 4.8
  • 4.8
  • 4.8
  • 4.8

4.8

6 ratings