Sost kilo

ች ግ ራ ች ን ፡ ም ን ፡ ነ በ ር ?


Listen Later

ሌላ ያልነገርኩሽ ፥ የልደትሽ ቀን አበባ ገዝቼ ነበር ። አዎ ! እኔ ። የሚገርምሽ ባገሩ እንደጠፋ ሁሉ የትናየት ሄጄ መሰለሽ ? መጨረሻ ላይ ወሰን ምናምን እሚሉት ሰፈር ትንሽዬ ኪዮስክ ውስጥ ትልቅ መቀስ የያዘች ሻጭ አየሁ ፤ ፈንታቸው መርገፍ የሆኑ ቅጠሎችን እየከረከመች።
እንዲሁ ልጅ ሳለሁ ፥ ከትምህርት መልስ ሙሽራ የሚሉትን አበባ ከሰው አፀድ ቀጥፌ ወደቤቴ እሮጥልሻለሁ ። ቤት ልደርስ 'ከባቢ እጄ ከአበባው ተሻሽቶ ኖሮ ፥ ወየበ ። ከቆረጡት ኋላ ቶሎ የሚሞት አይነት ዘር ሆኖም ይሆናል ። ብቻ እጄ ላይ ከስሞ ፥ ነደደኝ ።
የቀጠፍኩት እንዲያ እንዳማረበት ለ'ናቴ ልሰጣት ነበር ። ያም ሆኖ አልተውኩትም ። ከስራ መምጫዋን ጠብቄ (አስራ ሁለት ሰዓት እንደምንም ሞልቶልኝ) ሰጠኋት ። የኔ ንጉሥ ብላ አቀፈቺኝ ፥ ከመቀበል ያለፈ ቁብ ሳትሰጠው ። ጭራሽ ወርውራው መክሰስ መብላቴን እየጠየቀች ወደቤት ይዛኝ ገባች ። እጄን ይዛኝ ስትዘልቅ ፊቴ ወደወደቀው አባባ እንደዞረ ነበር ።
እናልሽ ቤሎንዥ...
ኪዮስኩ ውስጥ ያለችው ልጅ የሚቀባውን ነገር ቀብታ የሆነ የሚነፋ ነገር'ም ነፍታበት አጋጊጣ ምናምን ሰጠችኝ ። እንዴት እንዳማረበት ። ገዝቻት ስወጣ አመስግኜ ፥ መልካም በዓል ! አልኹ ። የምን በዓል ደሞ ? በሚል ግርምታ ታየሁ ፥ ሃሃ።
እዝነ ገመዴን ከጆሮዬ ስላልተነሳ ዘፈን እንደምሰማ ሁሉ ምንም ሳልል እግሬን አዙሬ መንገዴን ጀመርኩ ። ለካ ሌላ ሰው የአንቺን ልደት አይቀድስም ። የለም? ፥ ለካ የነሱ ካለንደር በንግስሽ ቀን አይዘጋም ።
ከናቴ ለጥቆ አበባ ልሰጠው የነበረው ላንቺ ነበር ። የገዛሁት አበባ በትራንስፖርት ግፍፊ እንዳይጎዳ ወክ ማድረግን መረጥኩ ። አበባውን እንደያዝኩ ይዤ በቀትር ስንከላወስ አላፊ መንገደኛ እያየኝ በልቡ የሆነ ነገር ይላል ። መቼም አበሻ "ምኗ እድለኛ ነች ፥ አበባ የሚሰጣት " ማለት አይቀናውም ። ...አ...ዬ ባህላችን.. ገለመሌ ...እያሉ ይሆናል ።
ሰባት ሰዓት ላይ የሜክሲኮው ቶታል (ቦንዡ ካፌ) ደረስኩ ። ተረከዜን ከማቃጠል ውጪ በጉዞው ብዙ አልተሰማኝም ። ትዝ ይልሽ ከሆነ አራቴ ስደውልና በአምስተኛው ጥሪውን ስትጠረቅሚው ፥ እዛ ቁጭ ብዬ ነው ። ከተቀመጥኩ ሰዓት ሊደፍን ምናምን ደቂቃ ሲቀረኝ ያ...!...ሜሴጅ ገባ።
- Sorry, Je ne peux pas venir.
መምጣት አልቻልኩም ። እንደው እንደቀላል ፤ የአንድ ግድንግድ መፅሀፍን ግፍ በአንድ ነጠላ መስመር ። አለ አደል ፥ ሲቻኮሉ ከሰው ተገጫጭተው ይቅርታ እንደመጠየቅ አይነት ያለ ።
እና አበባው ሳይደርስሽ ከእጄ ቀረ ። እናቴም ያኔ አበባውን ስሰጣት እንዴት ሆኜ እንዳመጣሁት አልጠየቀችም ። ማለት ፥ ስላልጠየቀች ለመቅጠፍ የከፈለኩትን መስዋዕትነት አልተረዳችም ። በልጅ ሩሄ አበባ ያህል ነገር ከሰው አጥር ላይ አርጄላት ፥ በቅጡ እንኳ አልባረከችኝም ። ከንቱ ድካም ነበር ። አበርክቶቴ መገፋት የጀመረው ከያኔ አንስቶ ነው ፤ እርኩስ እንደሚሠዋው በግ ፥ እሳት ከራማ ወርዶ እንደማይበላው ...።
የዛን ቀን እራሮቴ ተፈቅፍቆ ከልቤ አልወድቅ አለኝ ። የልደትሽ ቀን ባለፈ በሆነኛው ቀን ስልኬን አውጥቼ መርዕዩ ላይ Qu'est-ce qui ne va pas entre nous , bel ange? ብዬ ፃፍኩ ። ችግራችን ግን ምን ነበር ...?
ችግራችን ፥ የፍዮሪ በእጄ ላይ መሞት ሳይሆን ፥ ተቀባይ ማጣት ነው ። አንዳችኝ ጉም ሰንጠቀን አንዳችንን ከህዋ ስናስስ ሌላችን ጣርማበር ጓሣ ውስጥ ለሽ ብለን ነበር ። በተራሽ ደሞ አንዳችን ባነን ሌላችንን ስናስስ የሂማልያ ክምር ጋርዶን ለአይን እንሰወራለን ።
መልሱን እያወቅሁ ያረቀቅሁትን ጥያቄ ላንቺ መላክ ?አልፈለኩም ። ከደመና በታች እንደቀረ ፀሎት ፥ ካፍ እንዳልወጣ ቃል ፥ እንዳልተኖረ ምኞት ፥ ሲባኑ እንደረሱት ህልም ፥ ደርሰው እንዳልሰበኩት ወንጌል ...
በድህሪት መደለዣ የፃፍኩትን የቃላት ድርድር አንድ በአንድ ከስልኬ መርዕይ ሰረዝኩ ። ሰሌዳው እስኪራቆት ፤ የመተየቢያዋ ከርሰር ግራዋን ሄዳ ውልብ ውልብ እስክትል። ፥ እ ...ን...ዲ..ሁ •••|
------------------------------------------------------------
ያ ል ተ ላ ኩ ፡ አ ም ስ ት ፡ ቴ ክ ስ ቶ ች [ M e s s a g e -1 ]
...more
View all episodesView all episodes
Download on the App Store

Sost kiloBy Leoul Zewelde

  • 4.8
  • 4.8
  • 4.8
  • 4.8
  • 4.8

4.8

6 ratings