…ጭንቀቴ… ድር እንዳጠመደው ዝንብ ነው ። ሸረሪቷ ካሁን አሁን መጣች እያለ እንደሚሳቀቅ … ክንፉን እያማታ… የትም እንደማይፈናፈን…
…ጭንቀቴ…ለወር ታህል ቋጥራ እንደሚሾትልባት ነብሰጡር ነው ። ማህፀኗ አልረጋ እንዳላት … ዘጠኝ ወር ርቆ … የምልጃዋን ማርያም … ማርያም እንደምትል …
ጭንቀቴ…ከእናት አባቱ ጥል አምልጦ እንደወጣ ህፃን ነው ። … የሚሮጥ መድረሻ የሌለው… ልጋጉን እየሳበ በለንባዳ አፉ እንደሚያለቅስ …
…ጭንቀቴ … ፈረሰኞች በሌት መጥተው ጎተራውን እንዳነደደቡበት መጤ ነው ። ነጋጠባ ውጣልን እንደሚባል … ከአመድ ክምር ላይ ተቀምጦ… በለበቅ መሬት እንደሚጭር …
…ጭንቀቴ… ደግመው ደጋግመው እንደደፈሯት ማቲ ነው ። በወሲብ ያጋሱባትን ስታይ ወደውስጥ ያነባችው እንደሚንጣት… ሽንቷ እንደሚሞቃት …
…ጭንቀቴ… የብርሃን መቅረዙን ሰም እንደሞላው ምስኪን ነው ። ከእንቅልፉ ሲነቃ አይኑ እንደተጋረደበት … ድንገት ማየት እንደተሳነው … ታውሮ ታገኘው እንደሚላተም …
…ጭንቀቴ… ምላሠ ጥቁር ረግሟት የሚያረክስላት ደብተራ እንዳጣች ጋለሞት ነው ። የነካችው ሁሉ አልሰምር ብሎ … ህይወቷ ቆሌ እንዳጣባት…
…ጭንቀቴ… ተፈርጆ እንደተያዘተ ግዞተኛ ነው ። ሊያርዱት አንበርክከው የኋሊት እንደጠፈሩት … ከገላው ላይ የሥለት ንኺ እንደሚጠብቅ…
…ጭንቀቴ … ከጠባቂዋ ባልጋ የወር አበባዋ እንደቀረባት ልዕልት ነው ። የአባቷ ዘውድ እንዳይሰደብ መታነቂያ ቃጫ እንደምትፈትል … ነብሷን ልትሸኝ አንድ ሐሙስ እንደቀራት…
…ጭንቀቴ… እንደወደቀ የክፍል ተማሪ ነው ። ተከልሶ ከጓደኞቹ ኋላ እንደቀረ … እንደፈራ መስከረም እንደደረሰበት…
…ጭንቀቴ… ደመና አልፎት እንዳይሄድ እንደሚፀልይ ገበሬ ነው ። ረሀብ ሊፈጀው ጥፍሩን ስሎ እንደመጣበት … የቀበረውን ዘር ቆፍሮ ሊቅም እንደተቃጣ …
…ጭንቀቴ… እርሙን እወድሻለው ብሎ …እሺ… እንደተባለ አፍቃሪ ነው ። " እሺ " ደግሞ ምንድነው እያለ እንደሚብሰለሰል … ስሜትሽን ማወቅ ሽቶ ፥ እንዳልተነገረው …የተወሰደበት …እንደማይሰጠው … መጨነቄ መች ገባሽ ።