ብዙ ግዜ እግሮቼን ይዞ የሚያስቀረኝን ማጥ የማቦካው እኔ ራሴው ነኝ ። ለዚህም ነው ድብርቴን ያመጣው ጭጋጉ ይሁን ጭጋጉ የመጣው በኔ ድብርት እርግጠኛ ያልሆንኩት ።
በየግዜው የሚነሱብኝን ወጀቦችን እያሳለፍኩ እቆያለሁ - እኖራለሁ ለማለት እንኳ ትንሽ ይከብደኛል ። በአጭሩ ህይወቴ በረከት ርቋት ድንገት የሚወርድ ሲሳይ መጠበቅ ከጀመርኩ ቆየሁ ።
ሰማዩ ገና ማስገምገም ሲጀምር ከጀርባዬ ያለውን መጋረጃ ለሁለት ከፍዬ ወደላይ አንጋጠጥኩ - ዳመናው ፅልመት አዝሏል ። አከታትሎ መብረቅ ወረደ ። ሁሌ አይቶ እንደማያውቅ ያስበረግገኛል ። ፀሃፊዬ " ድምፁ እኮ ዘግይቶ ነው የሚደርሰው ፤ መፍራት ያለብህ ብርሃኑን ነው " ስትለኝ ይሰማኛል ። የያዝኳቸውን ወረቀቶች መሳቢያዬ ውስጥ ሸጉጬ ተነሳሁ - ለፊዚክስ የሚሆን ግዜ አልነበረኝም ።
መንገዴን ስጀምር . . . ዣንጥላ የያዙትም መኪናም የሚነዳውም ወራሪ እንደመጣ አይነት እኩል ይሮጣሉ ። ሱቆች የበረንዳ መከለያ ላስቲካቸውን ለመወጠር ይታገላሉ ። የነጎድጓዱን እሩምታና የሰውን ሁካታ ሽሽት የጆሮ ማዳመጫዬን ወትፌ ድምፁን እስከ ገደፉ ጨመርኩ ።
በፊት እንዲህ ሲዘንብ - በመስኮቴ መስታወት ላይ ተለጥፈው የሚወርዱ ጠብታዎችን አፍዘውኝ ከእውን አለም እሰለባለሁ ። ከቅጠሎች ላይ ተንሸራተው እቁር ረግረግ ላይ ሲያርፉ የሚፈጠረውን ዜማ በተመስጦ አደምጣለሁ ። አፈር ሲርስና ባክቴሪያዎች ሲዋሰቡ ያለውን ሽታ እየማግኩ በአርምሞ አምማለሁ ።
የገረጣው አየር በውን የማላውቃትን ቀይ ልጅ ያስናፍቀኛል ። ምኑን እንደማስብ እንጃ ! ብቻ በሌለ ትዝታ ጭ. ል . ጥ እላለሁ ።
በስሱ የጀመረው ካፍያ እየባሰና የአስፋልቱ ክፍተቶች በውሃ እየተሞሉ መጡ ። እየበሰበስኩ ቢሆንም ከአረማመዴ የተጨመረም ሆነ የተቀነሰ ፍጥነት የለም ። የለኮስኩት ሲጋራ ከንፈሬ ላይ በስብሶ ሳያልቅ በፊት አሽቀንጥሬ ጣልኩት ። ዛሬ ግን እንዴት እንደሌላው ግዜ ሮጬ አልተጠለልኩም ?
ጭራሽ እንዳበደ ሁሉ እጆቼን ዘረጋሁና ፊቴን አስጥቼ ዝናቡን እንደአመጣጡ መቀበል ጀመርኩ ። ንፋስ በማይረብሽ ፉጨት አብሮኝ ይሽከረከራል ። ጉንጮቼ ላይ የሚያርፉት ደቃቃ ዘለላዎች እየነጠሩ ይወድቃሉ ።
መሃል ጎዳና ላይ ጭንቀቴ እንደእድፍ ከላዬ እየታጠበ ሲፈስና ያልጮሁኳቸው እልፍ ፀሎቶቼ ሲመለሱ ተሰማኝ ። ውሃ እንደተጠማ የበረሃ ሜዳ ረሰረስኩ ፤ ስንጥቆቼ ገጥመው ፍቅር ወደውስጤ ሰረገ ። እንደልጓም ቆልፎ አላላውስ ካለኝ ፍርሃት በነፃነት ስጋፈጥ በጭጋግ ውስጥ ስፈካ ተሰማኝ ።
መኖር - ወጀቡን ተሳቀህ ስለማሳለፍ ሳይሆን በዝናቡ ውስጥ እንዴት መደነስ እንዳለብህ ስለመማር ነው ! . . . እንዲሉ ።