ነብሴን በገዙኝ ማግስት የፀሓይን ሞት አረዱኝ ። በከባድ ምጥ ማለፏን እንደሰማሁ በዛለ ጀምበር ወደ ለቅሶው ሄድኩ። መቃብሯ የጀበል ቓፍ (*የምድር ጠርዝ) ኮረብቶች ላይ ነው ።ለቀሥተኛው እየተነዳዳ ወደ ቀብሩ ይግተለተላል። እንደህፃን እግር እየተከተልኩ መጓዝ ጀመርኩ።
በገፍ ከሚጋዘዉ ለቀስተኛ እንባ የሚወጣኝ አንድ እኔ ነኝ ። ሌሎቹ የአይን መቅደሳቸው ተገልብጦ ከነጩ መቃድ የጠለሸ ደም ይፈሳል ። ዶቃ ብሌናቸው በቦታው የለም ። ወዮታቸውን ባልሰማም ከደረታቸው የሚነሳ ተደጋጋሚ ስቅታ ግን አለ።
እየሄድን ነው ። ከፊቴ የቀደሙም ሆኑ ከጀርባ የተውኳቸው ለቀስተኞች አናታቸው የተመለጠ ሲሆን ከአናታቸው ዙርያ እንፋሎት ይጤሳል ። በተገኘ የገላቸው ቦታ የሞጀጁ ህፃናት ተፈናጠውበታል። የፈላዎቹ አናትም እንዲሁ የተላሰ መላጣ ነው ። ጉዟችን የለቅሶ ነው እንዳልል የምሰማው ዋይታ የለም ። ልንሀጅጅ እንዳይሆን ሀዲስ አይቀራም ። ልቤ ብቻ በጨዋ ሹክሹክታ … ” ዒብሊስ ሊጎርስህ ነው ፣ አምልጥ…አምልጥ ! ” ይለኛል ።
(ש) እሣት ፥
ፀሓይ ምሽትን ልትወልድ ያማጠችበት ራማ (ሰማይ) በደም’ዳምና ጨቅይቶ ሰልሟል ። የእንግዴ ልጇ ጨረቃ ግርዶሽ ከልቷት ከእሳት ፣ ከአየርና ውኃ እንደታባች ነው ። መደበቋ ፀሓይን ላለመገነዝ የክህደት አይነት ነው ፤ ያለርሷ ሁለት ለሊት ትቆይ ይመስል ።
ገፊዋ ” ምሽት ” ስትማጥ ቆይታ ልክ እናቷን እንደገደለች መዳህ ጀመረች ። የሌቱ ንጉሥ በዙፋኑ ተሰይሞ ማህፀን ቀዳ የወጣችውን ዲቃላ እያየ ነው ። እኔ በርሷ እርጥብ ሽል ውስጥ ነኝ ።
(מ) ማይ ፥
በጫካው ስንተም ባዶእግራችን ከሚኮረሻሽመው ርጋፊ ቅጠል በቀር የሚያሰማ ድምፅ የለም ። አልፎ አልፎ ብቻ የሻሿ ንፋስ ይፎጫል ። ተጓዦቹ የገረጣ ፊት ተሸክመው ሲራመዱ ላየ ቅጥባቸው ሳይሞላ አስክሬን የሆኑ ይመስላል … ሰከም ደርግፍ … ሰከም ደርግፍ… ደግሞ ሰከም …
ዳገቱን ስቧጥ እንዲደግፈኝ መቋሚያ ይዣለሁ ። በዛም ያለድካም እያቀናሁ ነው ። እንዲ በደመንሚን ስንንጋ’ጋ ከተገተረ ዛፍና ጅብራ የሚጋጭ አልነበረም ። ሁለቱ አይኖቼ የሥውሩን ያህል እርባን የላቸው ይሆን ?
በተጓዦቹ ፊት ላይ ላብ ከደም ጋር ተለቁጦ ይንፎለፎላል ። ወደፊት እንጂ እርስ በርስ መተያየት የለም ። ከአሸን ህዝብ መሀል ምንም ያልሆንኩት እንዳሻኝ መዞር የምችለውም እኔ ብቻ ነኝ ። ከነሱ የነሲብ ህመም የኔ ደህና መሆን አስፈርቶኛል … ፈ …ራ …ሁ … !
መሀል መሀላችን የሚልከሰከሱት ውሾች ያነጥሳሉ ። ነብሷን ይማርና አክስቴ የከልብ ንጥሻ ሟርት ነው ትል ነበር ። እሱን ይዤ ጉዞው የመልካም አይሆን ? አልኩ … ወየት እየተነዳህ ነው? ውስጤ ተደርቦ ይጠይቀኛል … ውስጤ እንዲ ነው ክረምቱ ወጥቶ ሲያበቃ አትዘራም ነበር ? የሚል አይነት … አብረን ሄደን ከረፈደ ራሱን የሚያፀዳ …ጣዲቅ ።
ንጥቀት ይገትረኝና ስቆም በተቃራኒዬ ከሚጎርፈው ህዝብ እላተማለሁ ። እየፈዘዙ መገተር ካቲዬን በተራማጅ አውራ ጣት ማስቀጥቀጥ ሆነ ። እስከቃንዛዬ ለመቆም ሞክሬ አልቻልኩም ። በዚ ጉዞ መመለስም መቆምም አይቻልም ፣ የሩቅ አሥማት ድግም ነውና ተያይዞ ብቻ እንደመልካ መፍሰስ …
አንድ ነገር ገብቶኛል ። በዘፍጥረትና በምፅዓት … በመወለድና ሞት … በመጀመሪያና መጨረሻ … ባለ ሲባጎ ላይ ቆሚያለው ። ሚዛን ጠብቆ መጓዝ እንጂ ይሄም ያልፋል ብሎ ነገር የለም ። እዚህ የግዜ ጠለል ብሎ ነገር የለም … ሰዓትና ቁጥር ውሸት ነው ።
ጉብታውን እየተገፋፋን ወጥተን ወደኮረብታው ጫፍ ደረስን ። ጣቶቼ መሀል የላበኝ ላቦት በርዶ ቁር እየጠራ ነው ። ፈርቻለሁ … በጌታ ስም … በጣም ፈርቻለሁ ።
(א)አልፋ ፥
እንደደረሰን አንዳንዶቹ ረገዳ (*የለቅሶ ጭፈራ) ጀመሩ ። ሁለት እርምጃ ሄደው እንጠጥ እያሉ እንደመርገፍ ፤ ምን ይሉት ትዕይንት እንደሆን እንጃ ። ለጥቀው የተሸከሟቸውን ብላቴናት የተቦረቦረ ጉድጓድ ውስጥ ይዶሏቸው ገቡ ። ልጆቻቸውን እየገበሩ መሆኑ ነው ።
ከገደሉ ጀርባ ባለ ሸለቆ አካይስት ሲንጫጩ ይሰማል ። ወርአበባ ያላዩ አጎጠጎጤዎች ዘነዘና ይዘው የተጣሉትን ማቲዎች ያልማሉ። ሲወቅጧቸው እየዘመሩ ነው ..
ኻዩዬ ..
የፀደይ ሲሣዬ
ላንተ ለሌቱ ጌታ
ቃንዛ እስክሥ በኹሉ ፈንታ
(እሽም…
ምህረት የለም…)
ዝንተ’ዛዜል
ዝንተ ኅቡኣት
አጋናኤል ኽስባዔል ስውራት ።
(እሽም…
ምህረት የለም…)
ኦ…! ዔል
ናጴር ቆርጴል ።
(እሽም…
ምህረት የለም…)
ረሐቅ… ሳዶር
ረጅ.. አላዶር
(እሽም…
ምህረት የለም…)
ድንጋጤ ዋጠኝ ፤ እይዝ እጨብጠው አጣሁ። ለንሰሃ ብጮህ የምታይ አይመስለኝም … ጥቁር ጉም ወርዷል … እንዳልመለስ ከእውነት አገር በሺ እርፍ ርቂያለው ።
ከተራራው ጉልላት ላይ አንዲት ሴት ትታያለች ። ለሌቱ ንጉሥ ሚስቱ አትመስለኝም ፤ እንደ ንግስት ሲያረጋት አላየሁም ። በማርያም ጣቷ ላይ ሴንኬቶ ተቀልብታለች ። ፊቷን ጭምብል ከድኖት አይታይም ። በሚወቀቱት ልጆች ምት ፀጉራን እያሾረች ሹቢሣ ትደነክራለች ። (ሹቢሣ አንገት የማሽከርከር ጭፈራ ነው ።)
ደይን (ሲዖል) መድረሳችንን እንዳወቅሁ በሰነፍ አወራወር ጉልበት አጥፌ ተንበረከኩ ። እምነቴ በመንጠፉ መሸነፌን እንደ ማመን … ግዞቱን አሜን ብሎ እንደመቀበል ።
እንደተንበረከኩ ከኃኖስ ቃላይ ጠበል ዘነበ ። ጠበሉ ሲዘንብ ፣ ሴቲቱ ጭምብሏን ስታወልቅና ፀሓይ ስትወጣ አንድ ሆነ። ምሽት እንዳሰብኩት ብዙ ይዛኝ አልሄደችም ። ገና እግሯ ሳይጠና ፀሓይ ደምቃ ወጥታለች ። አታለውኛል … ፀሐይ አልሞተችም ።
አጃቢዎቼ አይናቸው ሲመለስ የኔ በተራው ለመገልበጥ መርገብገብ ጀመረ ። መራመድ ጀምሪያለው ፣ እየታየኝ አይደለም …አይኔ ተገልብጧል ። የተፈረደባቸው ሲድኑ እኔ ሳልሠረይ ቀረሁ ። በመጨረሻ ቃል ነበር … የተሸጠ ነበስ አይመለስም ።
( ክፍል አንድ)