ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ያጸደቀው የተራዘመ የብድር አቅርቦት የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ያሉበትን ሥር የሰደዱ ችግሮች ለመቅረፍ የተወጠኑ አምስት የፖሊሲ አላባዎች አሉት። የገቢ እና የወጪ ንግድ ሚዛን ጉድለትን ለማረቅ እና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ ይገኝበታል። የተራዘመ የብድር አቅርቦት የተሰኘውን መርሐ-ግብር ለማስፈጸም የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ለኢትዮጵያ 3.4 ቢሊዮን ዶላር ብድር አጽድቋል። ዓለም ባንክ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር እና እርዳታ ሰጥቷል።