የአውሮፓ ኅብረት ደን ተጨፍጭፎ የሚመረቱ ሸቀጦች ወደ ገበያው እንዳይገቡ ለመከልከል ያወጣው ሕግ የኢትዮጵያ ቡና አምራች ገበሬዎች ማኅበራት እና ላኪዎችን አስግቷል። ባለፈው ሰኔ የጸደቀው ሕግ ከኢትዮጵያ ቡና የሚገዙ የአውሮፓ ኩባንያዎችን ገና ካሁኑ እያሸሸ ነው። ከምታመርተው ቡና 30 በመቶውን ወደ አውሮፓ የምትልከው ኢትዮጵያ በሕጉ የተቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ ካላሟላች ትልቅ ገበያ ልታጣ ትችላለች።