Sost kilo

Sost kilo

By Leoul ZeweldeFiction
Download on the App Store

Sost kilo episodes

  • ያ ን ፡ ቀ ን ፥ ባ ታ ቆ ላ ም ጪ ኝ ስ ?
    ያ ል ተ ላ ኩ ፡ አ ም ስ ት ፡ ቴ ክ ስ ቶ ች [ M e s s a g e -2 ] .... ከወፍራም ብርጭቆ ላይ እያበረደች የምትቀምሰው ወተት የከንፈሯን ዳር በስልባቦት ይኩላል ። የአፏን ወተት ለመግፈፍ እጄን ሰድጄ ግልፋፊውን በጣቴ አስቀረሁ ። ያስቀረሁትን ቀመስኩ ። የላስኩትን ኬሚስትሪ ጣዕም ለማስረዳት ይቸግራል ። ሀይድሮጅን ደርድረው በቦንድ ቢስሉት ዘርፉ ከአሮጌ ዋርካ ይገዝፋል።
    ቤሎንዥ ፥ ዛሬ ንጋት ላይ ከፓሪስ-ቻርል የገባች ነው ። ስለሚደክም ፥ ችላ የምትመጣም አልመሰለኝም ነበር ። ለገሃር ሳባ ኬክ ቤት ተገናኘን ። ሳፊ ወተት ጋበዝኳት ። ግብዣው የይቅርታ ነው ። ከአምስት ቀን መዘጋጋት በኋላ የሀቅ ኩርፊያዬን ካድኩ ። ጥፋቱ የርሷ ሆኖ የይቅሩ ምንጭ የፈለቀው ከእኔ ነው ። ለምን ? ለሚል ጠያቂ ፥ በቃ ተፈጥሮ አንድ ህግ የላት (አጭር ቀጫጫ መልስ ፥ ሃሃ) ።
    ጉንጬን ነፍቼ ለጠፉት ውድ ቀናት ራሴን ገስፄ ፤ ማሪኝ አልኹ ። ኩርፊያ የአፍቃሪ ወጉ ቢሆንም ለርሱ አልታደልኩም ። ኩራቴን ገርስሼ ...የኔ ቤሎንዥ ፥ ስላጠፋሽ መልሰሽ እኔኑ ማሪኝ ፥ ከወዲህ አትያዢብኝ ...አልኩ ።
    ማህተም ሳያገኙ ልብን ከሰጡ እንዲ ነው ፤ የቁልቋል ማሳ ውስጥ እንደለቀቁት ፊኛ ። ካሁን አሁን እሾህ ወጋብኝ እያሉ ንፋስን ሲማፀኑ እንደመኖር ። ጧ'ን ላለመስማት ጆሮን ከድኖ በነሲብ እንደመከተል ። ዉል አልባ አፈቃቀር ፥ ተሳደው የሚያሳዱት ፍቅር።
    ታድያ ግን ያነጫንጫል ። መነጫነጩ ብዙ ሳይበስል እንደዛሬው በውስጥ ተግሳፅ ይሻራል ። ሽረቱ ርትዕ ስላልሆነ ቁስል ይተዋል ። ቁስሉን ደግሞ ...ቁ...ል...ም...ጫ...ያክመዋል ፥ ያው ከጠባሳ ባያድንም ።
    የኔ ቤሎንዥ በቃላት መጮት ትወዳለች ። የቃሎቿ አያይዛ ትርጉም የምትመሰርተው በፈገግታዋ እርጥበት ነው ። ሁለት ነጥብ ይሉትን ስርዓተ ነጥብ ለእንደኔ አይነቱ ፋራ ይተውታል ። የምትመሰርተው ንግግር ከደራሲ ተረክ ይረቃል። ደብተራ ፍቆ ቢደግምባቸው ከሰማይ አንድርቢ ያወርዳሉ ። መሳፍንት ድምፇን ተውሰው ክተት ቢያውጁ ዲዳ እንጂ ማንም አይወሰልትባቸውም።
    ከሁሉ ስሜን ስታቀብጥ ደስ እሰኛለሁ ። ቀድሳ ስትጠራው እንዳጣፈጠኝ በታምቡሬ ልሞ ይወርዳል ። ሲወርድ ከሆዴ የታፈነው መውደድ እንደቫይረስ እየተጋመሰ ራሱን በራሱ ያበዛል ።
    መጀመሪያ አቆላምጣ የጠራቺኝ የዛሬ ዓመት ክረምት ፥ በስልክ ሽቦ ወስጥ ነው ። በቅጡ አልሰማኋትም ፥ ደረቴ ተረብሾ መሸከም አቃተኝ ። ላይፈነዳ ነገር እየተብላላ አንጀቴ ውስጥ የሚፈላ ዩራንየም ሆነ ። ቤት ለእራት ስቀርብ የውስጤ ውሮ ወሸባ ከፊቴ እንዳይነበብኝ ፈራሁ ። እየበላን አባቴ ፊት መዝለል ሁሉ አሰኝቶኝ ነበር ፥ሃሃ ።
    ከእጄ የነበረው መፍትሄ ሳይክሌን ይዞ ከቤት መውጣት ነው ፤ ወጣሁ ። እንደጣቃ ጠቅልዬ ያፈንኩትን ስሜት አስፋልት ላይ በትኜ ፥ ወዴት እንደሆነ ሳላውቅ ፥ በሰርክ ውርጭ እየተገረፍኩ ፥ መሪዬን ለቅቄ ስሟን እየጠራሁ ... ጋ... ለ... ብ... ኩ ... ። ሄጄ-ሄጄ የማላውቀው መንገድ መሃል ሰስደርስ ድንገት ወደ ራሴ ተመለስኩ ፥ አማትቤ እየዘነበብኝ ወደቤት ስመለስ ትንሽ ቀዘቀዝሁ።
    የካፌው ጫጫታ (የወራሪ አንበጣ ድምፅ አይነት ጥዝታ) አልረበሸንም ። በኩርፊያዬ የመጣ ኩርፊያዋን ማሳረጊያ ብዙ አወራን ። ደሞ ብዙ ዝም ብለን ተያየን ፤ አይኖቻችን ውሃ አዝለው እስኪያንፀባርቁ። በዝምታ ስታየኝ ከአርያም ወድቃ መሄጃ እንደጠፋባት መሊክ ነው ። መተያየቱ እንዳበቃ ስፈራ የኖርኳቸውን ሚስጥራት ለመንገር ወሰንኩ ።
    እንደፋርሰ ዕፅ ህቡዔን ምን እንዳጦዘው እንጃ ሌላ ግዜ የሚከብዱኝ ሶስት ቃላት እንደነገሩ ተወረወሩልኝ ። ከቤሎንዥ ጋር የሚለየን ይሄ ነው ። አያሳስበኝም እንጂ (ወይ ማሰብ አልፈልግም) ከርሷ ቃል ላይ ሁሌም ነብስ ይጎድላል ። ቃሎቿ ቢያምሩም ፥ እዛው አፏ ውስጥ ነው የሚጋገሩት ። እዛው ተመርቶ ከሰዓት መርካቶ ሃሃ
    ብዕሬ ሶስተኛውን ከስኒው ስር በነበረ ቅዳጅ ሶፍት ላይ ደምቶ እንደጨረሰ 'ኦ! መሄድ አለብኝ' አለች ። ሁለቱን በቅጡ ያየቻቸው አልመሰለኝም ሶስተኛው 'Moi-même a besoin de toi' ...ቤሎንዥ ፥ ታስፈልጊኛለሽ የሚል ነበር ። እሱን በደንብ አይታዋለች ።
    -ትንሽ አትቆዪም ? አልኹ ለአመል
    -ኖ ፥ ሌላ ቀን ። አሁን ልሂድ
    ውስጤ እንሂንም ደቂቃዎች ከሱ ቀንሳ የሰዋችልህ እርሷ ሆና ነው ይለኛል ። ሌላ ግብዣ እንደሚጠብቃት አውቃለሁ ፥ የባሏ እራት ። ( ለካ ባል እንዳላት እስካሁን አልተናገርኩም ፥ የኔ ነገር )
    በባሏ አልቀናም ። አንድ ነገር ግን ይረገርመኛል ስማችን አንድ ነው ። ታዲያ ቀጥሎ ምን ያሳስበኛል እርሱንም ለኔ በሰጠችው ቁልምጫ ትጠራው ይሆን ? ... (አፍቃሪ አያስበው የለ)
    የቁልምጫዋ ስግብግብ ነኝ ። ከኔ ውጪ ማንም እንድትጠራበት አልፈልግም ። እናም አስባለው እሱንም እንደዛ ትለው ይሆን ? ... በሆነ ቀን የእጅ ስልኳን እንደያዘች እየተላፋን ነበር ። የስልኳ መተየቢያ ስሜን ሸምድዶ ኖሮ የስሜን የመጀመሪያ ቃል ስትጫን በራሱ ተሞላ ። ይታይ ፥ አሁን ሰው በዚህ ይደሰታል ? ልቤ በጮቤ የወር ቀለቡን ሰፈረ ፥ ጌታን ።
    Bonsoir ! ብላኝ እንደወጣች ከአይኔ እስክትጠፋ በካፌው ሻተር አሻግሬ ተከተልኳት ። አብራኝ እንድትሆን ብዙ ተመኝቼ ነበር ። ከሷ ሆኜ የምገድላቸው ሰኮንዶች ሰማይ ቤት ታስበው ቢቀነሱብኝ አይቆጭም ።
    እንዲህ ባሉ ቀናት ፥ ብቻዬን ስትተወኝ ውስጤ የሚቀረውን ስሜት አልወደውም ። የልቤ ዙርያ ይንቦለቦላል ። የት እሄዳለሁ ፍቅርን እንደረኛ ገሳ ለብሼ አልጠለለው ፥ ሮጬ አላመልጠው ነገር ።
    በአፍታዎች ውስጥ መልሶ ከፋኝ ። ሀድራዬ እንዲህ ነው ፍቅሬን ሳይሆን ማፍቀሬን ያስረግመኛል ። ልቤን የሆነ መካነ ልብ አዘጋጅታ ብትቀብረው አልኹ ። እንደዛ ሆኖ በወጣልኝና ያለእንባ የደስታ ጉንጉን ባስቀመጥኩ ።
    ካፌው ውስጥ ሳልንቀሳቀስ እንደደረቅሁ ለአራት ክፉ ሰዓታት ተቀመጥኩ ። አስር ደቂቃን ጮቤ ረግጦ ለሁለት መቶ አርባ ደቂቆች በልዕለ-እሳቤ ተወጋጋሁ ። ጉዳቴን መልሳ እንድታክመኝ አልፈለኩም ። ከሁሉ ቃላቶቿ ያስቀይሙኛል...ሜርድ ! ። ልነግራት ስልኬን አወጥቼ የመልዕክት መላኪያውን ከፈትኩ ።
    - Toujours à jouer avec les mots
    ቤሎንዥ ፥ ሁሌም በቃል ትጫወቻለሽ ።
    ማስወንጨፊያውን ከመጫኔ በፊት አሁን እንዴት ትሆን የሚል ሀሳብ ሰረቀኝ ። ከአቶ ባል ጋር እየተሳሳቁ ? እየሳማት ? ተኝተው ። ራሴ ለራሴው ሲያሰጣኝ ደግሞ በፀሊም ድምፆች ይቀጣኛል ። ለባሏ የነፈግከው ክብር ፣ የጣስከው ህግ ፣ የረገጥካት ሞራልን እያጣቀስክ አስብ እንጂ ...ሰልፊሽ ።
    የመላኬ የመጨረሻዎቹ ቅፅበቶች ላይ 'ስልኳ በርሱ እጀታ ላይ ቢሆንስ' የሚል ሀሳብ ገብቶ ነገሬን ቀያየረው ። ባሏ ቢያውቀኝና በወንጀሌ ባጣትስ ? እሳቤዬ እንደጎመዘዘኝ ዋጥኩ ። ሸምጋይ ጓደኛ እንኳ የለን ። ደሞ ኋላ በማን ላስለምናት ነው ? በእንዲ እንዲ ጣዖቴ እንድትቆጣ አልፈቀድኩም ። እየተጣሉ ማጣት አለመፈለግ ምን እንደሆነ እንጃ ፥ አላውቅም ። የተየብኳቸውን ፊደላት ግን አሟጥጬ ሰረዝኩ ። ቤ ሎ ን ዥ ፥ ታ ስ ፈ ል ገ ኛ ለ ች ።
    8 min
  • ች ግ ራ ች ን ፡ ም ን ፡ ነ በ ር ?
    ሌላ ያልነገርኩሽ ፥ የልደትሽ ቀን አበባ ገዝቼ ነበር ። አዎ ! እኔ ። የሚገርምሽ ባገሩ እንደጠፋ ሁሉ የትናየት ሄጄ መሰለሽ ? መጨረሻ ላይ ወሰን ምናምን እሚሉት ሰፈር ትንሽዬ ኪዮስክ ውስጥ ትልቅ መቀስ የያዘች ሻጭ አየሁ ፤ ፈንታቸው መርገፍ የሆኑ ቅጠሎችን እየከረከመች።
    እንዲሁ ልጅ ሳለሁ ፥ ከትምህርት መልስ ሙሽራ የሚሉትን አበባ ከሰው አፀድ ቀጥፌ ወደቤቴ እሮጥልሻለሁ ። ቤት ልደርስ 'ከባቢ እጄ ከአበባው ተሻሽቶ ኖሮ ፥ ወየበ ። ከቆረጡት ኋላ ቶሎ የሚሞት አይነት ዘር ሆኖም ይሆናል ። ብቻ እጄ ላይ ከስሞ ፥ ነደደኝ ።
    የቀጠፍኩት እንዲያ እንዳማረበት ለ'ናቴ ልሰጣት ነበር ። ያም ሆኖ አልተውኩትም ። ከስራ መምጫዋን ጠብቄ (አስራ ሁለት ሰዓት እንደምንም ሞልቶልኝ) ሰጠኋት ። የኔ ንጉሥ ብላ አቀፈቺኝ ፥ ከመቀበል ያለፈ ቁብ ሳትሰጠው ። ጭራሽ ወርውራው መክሰስ መብላቴን እየጠየቀች ወደቤት ይዛኝ ገባች ። እጄን ይዛኝ ስትዘልቅ ፊቴ ወደወደቀው አባባ እንደዞረ ነበር ።
    እናልሽ ቤሎንዥ...
    ኪዮስኩ ውስጥ ያለችው ልጅ የሚቀባውን ነገር ቀብታ የሆነ የሚነፋ ነገር'ም ነፍታበት አጋጊጣ ምናምን ሰጠችኝ ። እንዴት እንዳማረበት ። ገዝቻት ስወጣ አመስግኜ ፥ መልካም በዓል ! አልኹ ። የምን በዓል ደሞ ? በሚል ግርምታ ታየሁ ፥ ሃሃ።
    እዝነ ገመዴን ከጆሮዬ ስላልተነሳ ዘፈን እንደምሰማ ሁሉ ምንም ሳልል እግሬን አዙሬ መንገዴን ጀመርኩ ። ለካ ሌላ ሰው የአንቺን ልደት አይቀድስም ። የለም? ፥ ለካ የነሱ ካለንደር በንግስሽ ቀን አይዘጋም ።
    ከናቴ ለጥቆ አበባ ልሰጠው የነበረው ላንቺ ነበር ። የገዛሁት አበባ በትራንስፖርት ግፍፊ እንዳይጎዳ ወክ ማድረግን መረጥኩ ። አበባውን እንደያዝኩ ይዤ በቀትር ስንከላወስ አላፊ መንገደኛ እያየኝ በልቡ የሆነ ነገር ይላል ። መቼም አበሻ "ምኗ እድለኛ ነች ፥ አበባ የሚሰጣት " ማለት አይቀናውም ። ...አ...ዬ ባህላችን.. ገለመሌ ...እያሉ ይሆናል ።
    ሰባት ሰዓት ላይ የሜክሲኮው ቶታል (ቦንዡ ካፌ) ደረስኩ ። ተረከዜን ከማቃጠል ውጪ በጉዞው ብዙ አልተሰማኝም ። ትዝ ይልሽ ከሆነ አራቴ ስደውልና በአምስተኛው ጥሪውን ስትጠረቅሚው ፥ እዛ ቁጭ ብዬ ነው ። ከተቀመጥኩ ሰዓት ሊደፍን ምናምን ደቂቃ ሲቀረኝ ያ...!...ሜሴጅ ገባ።
    - Sorry, Je ne peux pas venir.
    መምጣት አልቻልኩም ። እንደው እንደቀላል ፤ የአንድ ግድንግድ መፅሀፍን ግፍ በአንድ ነጠላ መስመር ። አለ አደል ፥ ሲቻኮሉ ከሰው ተገጫጭተው ይቅርታ እንደመጠየቅ አይነት ያለ ።
    እና አበባው ሳይደርስሽ ከእጄ ቀረ ። እናቴም ያኔ አበባውን ስሰጣት እንዴት ሆኜ እንዳመጣሁት አልጠየቀችም ። ማለት ፥ ስላልጠየቀች ለመቅጠፍ የከፈለኩትን መስዋዕትነት አልተረዳችም ። በልጅ ሩሄ አበባ ያህል ነገር ከሰው አጥር ላይ አርጄላት ፥ በቅጡ እንኳ አልባረከችኝም ። ከንቱ ድካም ነበር ። አበርክቶቴ መገፋት የጀመረው ከያኔ አንስቶ ነው ፤ እርኩስ እንደሚሠዋው በግ ፥ እሳት ከራማ ወርዶ እንደማይበላው ...።
    የዛን ቀን እራሮቴ ተፈቅፍቆ ከልቤ አልወድቅ አለኝ ። የልደትሽ ቀን ባለፈ በሆነኛው ቀን ስልኬን አውጥቼ መርዕዩ ላይ Qu'est-ce qui ne va pas entre nous , bel ange? ብዬ ፃፍኩ ። ችግራችን ግን ምን ነበር ...?
    ችግራችን ፥ የፍዮሪ በእጄ ላይ መሞት ሳይሆን ፥ ተቀባይ ማጣት ነው ። አንዳችኝ ጉም ሰንጠቀን አንዳችንን ከህዋ ስናስስ ሌላችን ጣርማበር ጓሣ ውስጥ ለሽ ብለን ነበር ። በተራሽ ደሞ አንዳችን ባነን ሌላችንን ስናስስ የሂማልያ ክምር ጋርዶን ለአይን እንሰወራለን ።
    መልሱን እያወቅሁ ያረቀቅሁትን ጥያቄ ላንቺ መላክ ?አልፈለኩም ። ከደመና በታች እንደቀረ ፀሎት ፥ ካፍ እንዳልወጣ ቃል ፥ እንዳልተኖረ ምኞት ፥ ሲባኑ እንደረሱት ህልም ፥ ደርሰው እንዳልሰበኩት ወንጌል ...
    በድህሪት መደለዣ የፃፍኩትን የቃላት ድርድር አንድ በአንድ ከስልኬ መርዕይ ሰረዝኩ ። ሰሌዳው እስኪራቆት ፤ የመተየቢያዋ ከርሰር ግራዋን ሄዳ ውልብ ውልብ እስክትል። ፥ እ ...ን...ዲ..ሁ •••|
    ------------------------------------------------------------
    ያ ል ተ ላ ኩ ፡ አ ም ስ ት ፡ ቴ ክ ስ ቶ ች [ M e s s a g e -1 ]
    6 min
  • Intala mootii
    አባት ሆይ … !
    ፀልዬ አላውቅም - ብዙ እንዳትታዘበኝ ፤
    ዛሬን ብቻ… ጆሮ ዳባ ሳትል …
    ለሥጋዬ ውሉድ ፥ አንዲት ማቲ ዋጀኝ ።
    'ሴት' ሆና የማምናት ፤
    ካለ ሚስት አለናት ፥ አባት 'ምሆናት ።
    አንዲት ልዕልት ማቲ
    ሳይጋሩኝ የምወዳት - ሳትጋራ የምትወደኝ
    አቤቱ - በረቂዮትህ ዋጀኝ ።
    ጡት ብነሳ እንደማልጋ ላም
    ባላግት ፥
    ወተት ባላደማም
    ጀባ'ኝ እንጂ ፥
    እንደ'ዶሮ ጭሬ አፀድቃታለው
    ህይወቴ የሷ መንግስት ነው ።
    አባት ሆይ …
    ፀልዬ አላውቅም - ብዙ እንዳትታዘበኝ ፤
    ዛሬን ብቻ… ጆሮ ዳባ ሳትል …
    ለሥጋዬ ውሉድ ፥ አንዲት ማቲ ዋጀኝ ።
    2 min
  • ዝ ም ታ ህ ን ፡ ማ ረ ኝ
    በያንዳንዱ የእምነት ክሬ
    እንደሹራብ ተተርትሬ
    እንዳልጣፍ እንዳልሰፋ ሆኛለው
    የቀረኝ ጨርቅ ከቅዳጄ ያነሰ ነው ።
    የሲዖል መልህቅ ከግሬ ታስሯል
    እፍግ ሰንሰለቱ እሄድኩት ድረስ ይረዝማል
    ቁርጭሚቴ ካልቦ ያለረፍት ይንቋቋል
    ህልው ምልክቴ ጠፍረ ባርያ ሆኗል ።
    * * *
    ቀደም . . .በሌት ግርማ ታውሬ
    ስቀይርህ ሳፈስህ ከደምስሬ
    በፋኑዔል ክንፍ ሰበዝ
    ደምቀለም ነክሬ ነብሴን ላውሬ ስቤዥ
    ዝም ብለኸኛል !
    በካሚዮን ከሚንቦገቦገው
    በጥፍሮቹ ምድርን ቧጦ ከከበበው
    አይሆኑ ውዬ
    ለሌጊዮን ግዞት ስሸጥ በፊርማዬ
    ደግመህ ዝም ብለኸኛል !
    በዚ ዝምታህ
    ዘላለምን ንቄ ቀቢፅ አፍታን ቃረምኩ
    ባይኖር ነው ብዬ ውድ ነብሴን ገበርኩ ።
    * * *
    ጌታዬ
    አሁን ድንገት ዞሬ
    ከአፀድህ አስጠግተህ ከቀኝህ ደምረኝ
    ለማለት አቅም አጣሁ የግብዝ ንሰሐ መሰለኝ
    ነቀርሳዬ እንደው ስር ሰዷል
    ከጥፍሬ በቀር ገላሄ ሁሉ በሀጥ ነዷል
    አባት ሆይ . . .
    ሱባዔ ጠፍቶብኛል ፀሎት ካደረስኩ ቆይቻለሁ
    ልመና እንደማያውቅ ትኩስ ድውይ ፊትህ አለሁ
    ዝምታህን ሻረው እያልኩ በዝምታ አለቅሳለሁ
    ምሉእ ውስተ ኩሉ
    አመድ ሳልሆን አጥንቶቼ እንዳሉ
    ሥለማያልቀው የምህረትህ ፀዳል
    በትላንትዬና ዛሬ መሀል
    የነበረን ዝምታህን ማረኝ
    አቤቱ ማረኝና ፤
    አናግረኝ !
    2 min
  • Excerpt : እና ፥ እየዘነበ ነው . . .
    ብዙ ግዜ እግሮቼን ይዞ የሚያስቀረኝን ማጥ የማቦካው እኔ ራሴው ነኝ ። ለዚህም ነው ድብርቴን ያመጣው ጭጋጉ ይሁን ጭጋጉ የመጣው በኔ ድብርት እርግጠኛ ያልሆንኩት ።
    በየግዜው የሚነሱብኝን ወጀቦችን እያሳለፍኩ እቆያለሁ - እኖራለሁ ለማለት እንኳ ትንሽ ይከብደኛል ። በአጭሩ ህይወቴ በረከት ርቋት ድንገት የሚወርድ ሲሳይ መጠበቅ ከጀመርኩ ቆየሁ ።
    ሰማዩ ገና ማስገምገም ሲጀምር ከጀርባዬ ያለውን መጋረጃ ለሁለት ከፍዬ ወደላይ አንጋጠጥኩ - ዳመናው ፅልመት አዝሏል ። አከታትሎ መብረቅ ወረደ ። ሁሌ አይቶ እንደማያውቅ ያስበረግገኛል ። ፀሃፊዬ " ድምፁ እኮ ዘግይቶ ነው የሚደርሰው ፤ መፍራት ያለብህ ብርሃኑን ነው " ስትለኝ ይሰማኛል ። የያዝኳቸውን ወረቀቶች መሳቢያዬ ውስጥ ሸጉጬ ተነሳሁ - ለፊዚክስ የሚሆን ግዜ አልነበረኝም ።
    መንገዴን ስጀምር . . . ዣንጥላ የያዙትም መኪናም የሚነዳውም ወራሪ እንደመጣ አይነት እኩል ይሮጣሉ ። ሱቆች የበረንዳ መከለያ ላስቲካቸውን ለመወጠር ይታገላሉ ። የነጎድጓዱን እሩምታና የሰውን ሁካታ ሽሽት የጆሮ ማዳመጫዬን ወትፌ ድምፁን እስከ ገደፉ ጨመርኩ ።
    በፊት እንዲህ ሲዘንብ - በመስኮቴ መስታወት ላይ ተለጥፈው የሚወርዱ ጠብታዎችን አፍዘውኝ ከእውን አለም እሰለባለሁ ። ከቅጠሎች ላይ ተንሸራተው እቁር ረግረግ ላይ ሲያርፉ የሚፈጠረውን ዜማ በተመስጦ አደምጣለሁ ። አፈር ሲርስና ባክቴሪያዎች ሲዋሰቡ ያለውን ሽታ እየማግኩ በአርምሞ አምማለሁ ።
    የገረጣው አየር በውን የማላውቃትን ቀይ ልጅ ያስናፍቀኛል ። ምኑን እንደማስብ እንጃ ! ብቻ በሌለ ትዝታ ጭ. ል . ጥ እላለሁ ።
    በስሱ የጀመረው ካፍያ እየባሰና የአስፋልቱ ክፍተቶች በውሃ እየተሞሉ መጡ ። እየበሰበስኩ ቢሆንም ከአረማመዴ የተጨመረም ሆነ የተቀነሰ ፍጥነት የለም ። የለኮስኩት ሲጋራ ከንፈሬ ላይ በስብሶ ሳያልቅ በፊት አሽቀንጥሬ ጣልኩት ። ዛሬ ግን እንዴት እንደሌላው ግዜ ሮጬ አልተጠለልኩም ?
    ጭራሽ እንዳበደ ሁሉ እጆቼን ዘረጋሁና ፊቴን አስጥቼ ዝናቡን እንደአመጣጡ መቀበል ጀመርኩ ። ንፋስ በማይረብሽ ፉጨት አብሮኝ ይሽከረከራል ። ጉንጮቼ ላይ የሚያርፉት ደቃቃ ዘለላዎች እየነጠሩ ይወድቃሉ ።
    መሃል ጎዳና ላይ ጭንቀቴ እንደእድፍ ከላዬ እየታጠበ ሲፈስና ያልጮሁኳቸው እልፍ ፀሎቶቼ ሲመለሱ ተሰማኝ ። ውሃ እንደተጠማ የበረሃ ሜዳ ረሰረስኩ ፤ ስንጥቆቼ ገጥመው ፍቅር ወደውስጤ ሰረገ ። እንደልጓም ቆልፎ አላላውስ ካለኝ ፍርሃት በነፃነት ስጋፈጥ በጭጋግ ውስጥ ስፈካ ተሰማኝ ።
    መኖር - ወጀቡን ተሳቀህ ስለማሳለፍ ሳይሆን በዝናቡ ውስጥ እንዴት መደነስ እንዳለብህ ስለመማር ነው ! . . . እንዲሉ ።
    4 min
  • 'ወድሃለሁ ስትይ - ስሜቱን ግን ታውቂዋለሽ ?
    . . . ምልዓተዓለም ፀጥ እንደሚል ፤ ልቤ የምር እንደምትታፈን ፤ እግሬ እንደሚቀዳደም ፤ ብሌኖቼ እንደሚሰፉ ፤ ሳይታዘዝ ጉንጬ እንደሚፈግግ ፤ እየሄድኩ መቆም እንደሚያምረኝ ፤ እየቆምኩ መሄድ እንደሚያሰኘኝ ።
    ዝለል ዝለል እንደሚለኝ ፤ ሸራ ጫማዬን ፈትቼ እንደማስር ፤ ስልኬን አውጥቼ ሳልደውል መልሼ እንደምከተው ፤ ሽቶሽ ከየትም እንደሚሸተኝ ፤ የት መሄዱን ሳላውቅ ታክሲ እንደምሳፈር ፤ በውጥንቅጥ መሀል አንቺን ብቻ እንደማስብ ፤ የምጠላው ሙዚቃ እንደሚመስጠኝ ፤ አልፎ - ደንስ ደንስ እንደሚለኝ ።
    ሀይል ገላዬን እንደሚወር ፤ ደረቴ እንደሚረበሽ ፤ ላለፈ ለማኝ ሁሉ መቶ ብር ስጥ-ስጥ እንደሚለኝ ፤ በቀን እንደማልም ፤ ይለወትሮ ቤተክርስትያን እንደምስም ፤ ሱቢህ ድረስ እንደማልተኛ ። እንደምከንፍ - ወለሉ እየራቀኝ - ኮርኒሴ እንደሚቀርበኝ
    እንጃ ! አለ አደል - ዝብርቅርቅ መሆኑን - ስሜቱን ግን ታውቂዋለሽ ?
    2 min
  • ለመውደቅ ግን ተሥፋ አለኝ •
    አንድ ልጇ ዱርዬ ሆኖ እንዳሸነፋት እናት … በካር ማህፀኗ ሌላ ዘር ሳይዝ … እሱኑ ስትል አሳድጋ… ሲያፄም ግዜ ከእጇ እንደወጣ… ደምላቧ ከንትቶ የምትኖርለት ሌላ ምክንያት እንዳጣች …
    ብዙ ብዙ ሄዶ እግዜርን ከቦታው እንዳጣ ቄስ … እድሜውን ሙሉ የቀራቸው መፃህፍት እርባን እንዳጡበት … ረፍዶ ከመመለስና ፣ ተሳስቶም ከመሄድ ምርጫ እንዳጣ … በሁለት የቂጡ ጉንጮች ሁለት ወንበር ላይ እንደተቀመጠ …
    … ተሥፋ አጥቻለው …
    አሳዳሪው አረጀህ ብሎ እንዳባረረው ውሻ ። እድሜ ዘመኑን በሳጥን ታጥሮ ኖሮ … ከግቢው ሲወጣ አቅም ከድቶት ቁጊያም እንደሆነ … የሰፈር ውሾች ሊነክሱ እንደሚያሳዱት …
    እድሜ ይፍታህ ታስሮ ድንገት በአመክሮ እንደማሩት ታራሚ … የሚሄድበት እንዳጣ… ከሰላሳ ዓመት በፊት ከሚያውቀው አገር መግባባት እንዳቃተው … መፈታት መታሰር እንደሆነበት …ወህኒ መመለስ እንዳማረው …
    … ተሥፋ አጥቻለው …
    … እና አልረካ ፥ የሚያረካኝ ነገር ጠፍቷል ። አልቀል ነገር ልጅነቴን ርቄዋለው … እንዳልተልም እምነቴ ባዶ ነው … በእንዲህ ራሴን የሀሰት ከመደገፍ የሃቅ መንሸራተቱ ይሻላል … ታኮዬን አንሱልኝ ፥ ተሥፋ ባጣም እንደምወድቅ ተሥፋ ላድርግ ።
    3 min
  • ጭንቀቴ መች ገባሽ
    …ጭንቀቴ… ድር እንዳጠመደው ዝንብ ነው ። ሸረሪቷ ካሁን አሁን መጣች እያለ እንደሚሳቀቅ … ክንፉን እያማታ… የትም እንደማይፈናፈን…
    …ጭንቀቴ…ለወር ታህል ቋጥራ እንደሚሾትልባት ነብሰጡር ነው ። ማህፀኗ አልረጋ እንዳላት … ዘጠኝ ወር ርቆ … የምልጃዋን ማርያም … ማርያም እንደምትል …
    ጭንቀቴ…ከእናት አባቱ ጥል አምልጦ እንደወጣ ህፃን ነው ። … የሚሮጥ መድረሻ የሌለው… ልጋጉን እየሳበ በለንባዳ አፉ እንደሚያለቅስ …
    …ጭንቀቴ … ፈረሰኞች በሌት መጥተው ጎተራውን እንዳነደደቡበት መጤ ነው ። ነጋጠባ ውጣልን እንደሚባል … ከአመድ ክምር ላይ ተቀምጦ… በለበቅ መሬት እንደሚጭር …
    …ጭንቀቴ… ደግመው ደጋግመው እንደደፈሯት ማቲ ነው ። በወሲብ ያጋሱባትን ስታይ ወደውስጥ ያነባችው እንደሚንጣት… ሽንቷ እንደሚሞቃት …
    …ጭንቀቴ… የብርሃን መቅረዙን ሰም እንደሞላው ምስኪን ነው ። ከእንቅልፉ ሲነቃ አይኑ እንደተጋረደበት … ድንገት ማየት እንደተሳነው … ታውሮ ታገኘው እንደሚላተም …
    …ጭንቀቴ… ምላሠ ጥቁር ረግሟት የሚያረክስላት ደብተራ እንዳጣች ጋለሞት ነው ። የነካችው ሁሉ አልሰምር ብሎ … ህይወቷ ቆሌ እንዳጣባት…
    …ጭንቀቴ… ተፈርጆ እንደተያዘተ ግዞተኛ ነው ። ሊያርዱት አንበርክከው የኋሊት እንደጠፈሩት … ከገላው ላይ የሥለት ንኺ እንደሚጠብቅ…
    …ጭንቀቴ … ከጠባቂዋ ባልጋ የወር አበባዋ እንደቀረባት ልዕልት ነው ። የአባቷ ዘውድ እንዳይሰደብ መታነቂያ ቃጫ እንደምትፈትል … ነብሷን ልትሸኝ አንድ ሐሙስ እንደቀራት…
    …ጭንቀቴ… እንደወደቀ የክፍል ተማሪ ነው ። ተከልሶ ከጓደኞቹ ኋላ እንደቀረ … እንደፈራ መስከረም እንደደረሰበት…
    …ጭንቀቴ… ደመና አልፎት እንዳይሄድ እንደሚፀልይ ገበሬ ነው ። ረሀብ ሊፈጀው ጥፍሩን ስሎ እንደመጣበት … የቀበረውን ዘር ቆፍሮ ሊቅም እንደተቃጣ …
    …ጭንቀቴ… እርሙን እወድሻለው ብሎ …እሺ… እንደተባለ አፍቃሪ ነው ። " እሺ " ደግሞ ምንድነው እያለ እንደሚብሰለሰል … ስሜትሽን ማወቅ ሽቶ ፥ እንዳልተነገረው …የተወሰደበት …እንደማይሰጠው … መጨነቄ መች ገባሽ ።
    4 min
  • •••ሥትናፍቂኝ
    ስ ት ና ፍ ቂ ኝ
    [ ል ዑ ል ፡ ዘ ወ ል ደ ]
    ስትናፍቂኝ …
    ባሏ ለዕድሜ ይፍታሕ ወህኒ እንደተወረወረባት ሴት ነው ። መልሳ ላታገኘው ነገር እሁድን እየጠበቀች እንደምትጠይቀው …
    ስትናፍቂኝ …
    ሲዖል ተኮራምቶ ገነትን እንደሚያልም ሠይጣን ነው ። ምህረት ሱሚ ሆኖበት በልቡ ማብከሪያ እንደሚለምን ። ጥፍሮቹን ቢከረክም'ም ርህራሄ ተነፍጎት ምናልባትን እንደያዘ…
    ስትናፍቂኝ …
    በምናብሽ የሚሄድ አስፋልት ሣይና በዛ ላይ በተቃራኒ አቅጣጫ የሚጓዝ ከንቱ ደሞ አስቢ ። እየሄደ የሚመስለው ግን አንድ ቦታ ላይ እንደቆመ ። ኃይሉ ሲሟጥ አስፋልቱ በራሱ አቅጣጫ እያንደባለለ እንደሚወስደው …
    ስትናፍቂኝ …
    ወደቀኝ እንደሚዞር ሽክርክር ሰዓት ነው ። የግዜ ጠለል ወደኋላ እንደሚነዳው ። ነገ የሚባል ነገርን እንደማያውቅ ። ትላንትን ሲገረብ እንደሚኖር…በዕስብታ …በትውስታ … በትዝታ …
    ስትናፍቂኝ …
    ጠምላይ ቅጠሎቿ ረግፈው ምግቧን በምን እንደምታዘጋጅ ግራ እንደገባት ሐረግ ነው ። ፎቶሲንተሲስ ቅንጦት ሆኖባት እግሯ መጠውለግ እንደጀመረ ። ፀሐይ ግልጥ ብላላት ደመንሚን እንደወረሳት …
    ስትናፍቂኝ …
    እግር ከወርች በወፍጮ ድንጋይ ተቋጥሮ በቀላይ እንደተጣለ ፍርደኛ ነው ። ቁልቁል ወደወለል እየሰመጠ አየር እንደሚያቡለቀልቅ ። ወደውስጥ መተንፈስ ተዓብ እንደሆነበት …
    ስትናፍቂኝ …
    ብሶል ( *ኮምፓስ )ሳይዝ እንደወጣ አሳሽ ነው ። ሁሌም ሰሜኑን እንደሚስት ። አቅጣጫ ሳይኖረው ዝምብሎ እንደሚሮጥ …
    ስትናፍቂኝ …
    በማማሰያ ተንጠፍጥፎ ቡሖን እንደሚለቁጥ አብሲት ነው ። ውሃ ሲያቀር ከርሞ የሊጥ ባህር ውስጥ ጭልጥ ብሎ እንደሚስጥም …
    ስትናፍቂኝ- እንደዛ ነው ። " ስትናፍቂኝ " እያልኩ የፃፍኩት ስናፍቅሽ ላለማለት ነው ። በኔ ማስታወስ ውስጥ መረሳት የሚባልን ኩሸት ማሰብ ሕማም ነው ። በስትናፍቂኝ ውስጥ ትናንፍቀኝ ይሆን ? የሚል ተሥፋ አለ ። አልዋሽሽም ትናፍቂኛለሽ ! ማለቴ እናፍቅሻለው … እየሄድኩ … እንደማንገናኝ እያሰብኩ … በዋልሴ ካራ ውስጤን እያጨድኩ ።
    3 min

About Sost kilo

From the publisher's feed

Stories.